human impact of internet shutdowns

#KeepItOn ግጭት፦ አማራ ክልል ውስጥ የኢንተርኔት መዘጋት በሰው ላይ የሚያሳድረው ጫና

Read in English

ይዘቱን የተመለከተ ማስጠንቀቂያ፦ ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው ጽሑፍ የጦር ወንጀልን፣ ወሲባዊ ጥቃትን፣ ነፍስ ግድያን እና ሞትን የተመለከተ ነው።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በአማራ ክልል ውስጥ ሙሉ በሙሉ ኢንተርኔትን እንዲቋረጥ ካደረጉ ከ 100 ቀናት በላይ አስቆጥሯል — ይህም በማን አለብኝነት የሚፈጸም የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው። ሐምሌ 27 ቀን በፌደራል የመከላከያ ኃይሎችና በአማራ ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ከተፋፋመ በኋላ ያለ ምንም ማብራሪያ የኢትዮጵያ መንግሥት የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎትን፣ የመሥመር ስልክ ግንኙነትን፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያንና WhatsApp፣ Facebook፣ እና X (ከዚህ ቀደም Twitter ይባል የነበረውን) የስልክ አማራጮችን ዘግቷቸዋል። የአማራ ክልል ነዋሪዎች እንዲህ ዓይነቱን መሰል በጅምላ የሚደረግ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ሲያጋጥማቸው በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው

እንዲህ ዓይነቱ ለረዥም ጊዜ የሚደረግ የአገልግሎት መቋረጥ ሰዎች ሕይወትን ሊያድን የሚችል መረጃን እንዳያገኙና በግጭትና በሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መካከል እንኳ ሆነው እርስ በርስ መገናኘት እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል። መስከረም ወር ላይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና የክልሉ ሚሊሺያ አማካይነት ሰዎች በዘፈቀደ እንደሚገደሉ፣ ወሲባዊ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙ፣ አካላዊ ድብደባ እንደሚከናወን፣ ሰዎች እንደሚፈናቀሉ እና የሲቪል ግለሰቦች ንብረቶች እየወደሙ እንደሆነ ሪፖርት አድርጎ ነበር። በቅርብ ጊዜ ማለትም ከሁለት ሳምንት በፊት ኮሚሽኑ ባሰራጨው ሪፖርት ደግሞ በድሮን በሲቪሎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃትን ጨምሮ ሁኔታው እጅግ ወደ የከፋ ደረጃ እየተባባሰ መሄዱን አመላክቷል። ይኸው የመጨረሻው ሪፖርት ከነሐሴ ወር ጀምሮ ብቻ እንኳን ቁጥራቸው ወደ 200 የሚገመት የአስገድዶ መደፈር ጥቃቶች መፈጸማቸውን በመጠቆም ወሲባዊና ጾታዊ ጥቃቶች ቁጥራቸው በሚያሳስብ ደረጃ እየጨመረ መሄዱን አፅዕኖት ሰጥቶ ሪፖርት አድርጓል።

የኢንተርኔት ግንኙነትን ማቋረጥ በጦርነት ቀጣና ውስጥ ያሉ ሰዎችን ስቃይ መጨመር ከመሆኑ ባሻገር የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተደባብሰው እንዲታለፉ የሚያደርግ ድርጊት ነው። እነዚህ ከዚህ በመቀጠል የቀረቡት 11 ታሪኮች በአማራ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ተማሪዎች፣ ነርሶች፣ ደላሎች፣ ኢንጂነሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የዩኒቨርስቲ አስተማሪዎች እና ሌሎች ከኅብረተሰቡ ከተውጣጡ አካላት የተገኙ ታሪኮች ሲሆኑ ከሌሎች ነገሮች መሃል በተለይ የኢንተርኔት አገልግሎቱ መቋረጥ ያሳደረባቸውን ከፍተኛ ጉዳት በጉልህ ያሳያል

የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት የማቋረጥ ድርጊቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲተው ለማስደረግ በምናደርገው ግፊት ላይ እርስዎም የበኩልዎን አስተዋፅኦ ያድርጉ እንዲሁም የኢንተርኔት መቋረጥ የሚፈጥረው ጫናን የተመለከቱ ከዓለም ዙሪያ የተሰበሰቡ ታሪኮችን እዚህ ላይ ያንብቡ።

ከአማራ ክልል ካሉ ሰዎች የተገኙ 11 ታሪኮች

ማስታወሻ፦ ለደኅንነት ሲባል የአንዳንድ ባለታሪኮች ስም እንዲቀየር ተደርጓል። ከዚህ በታች ያለውን ምስል ማየት ካልቻሉ በአሳሽዎ (ብሮውሰር) ላይ ያለውን የግላዊነት ማላቂያ እየሠራ ስለመሆኑ ያረጋግጡ። የተሻለ ማየት እንዲችሉ በዴስክቶፕ ላይ ፋይሉን ቢከፍቱ ይመረጣል።.

ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎትን በማቋረጥ ወንጀል በአፍሪካ ውስጥ ቀዳሚዋ አገር ነች

የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ በሰዎች ሕይወትና በተቋማት ላይ ሊቀለበስ የማይችል ጉዳት የሚያደርስ እንደመሆኑ እጅግ አሳሳቢ ነው። ሰዎች ኢንተርኔት አገልግሎትን እንዳያገኙ የማድረግ ድርጊት በቸልታ መታለፍ የለበትም። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ መንግሥት ያለው የኋላ ታሪክ አስቀያሚ ነው — Access Now እና #KeepItOn ቅንጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ከ 2008 ጀምሮ ብቻ እንኳ 26 የኢንተርኔት አገልግሎትን የማቋረጥ ድርጊቶች መፈጸማቸውን በማስረጃ ማረጋገጥ ችሏል። በዚህም አገሪቱ በዚህ የመብት ጥሰት በአፍሪካ ቀዳሚዋ አገር ሆናለች። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ይህን መጥፎ ልማድ ለማረቅ በአስቸኳይ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። 

አገሪቱ ቀውስ ውስጥ እያለች የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ኢንተርኔት አገልግሎት ማቋረጥን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀማቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ በምንፈጥረው ጫና ከዚህ በታች ያለውን መልእክት መልሶ በመጠለፍ እና ይህን ጦማር በማኅበራዊ ትስስር ገጾችዎ ላይ ለሌሎች እንዲደርስ በማጋራት Access Now እና #KeepItOn ቅንጅትን ይቀላቀሉ።

Access Now እና #KeepItOn ቅንጅት የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ የሚያስከትለውን ከፍተኛ ጉዳት ለማሳየት እና ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ በኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ የጉዳት ሰለባ የሆኑ ሰዎችን የግል ታሪክ መሰብሰቡንና ይፋ ማውጣቱን ቀጥሏል። ይህ ቅንጅት ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ከ ኢትዮጵያ ህንድባንግላዴሽ ቶጎካሜሮንታንዛኒያኡጋንዳ ኢራንታጂኪስታንካዛኪስታን እና ሌሎች አገሮች የተገኙ ታሪኮችን አትሞ አሠራጭቷል።

የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ወንጀል ሰለባ የሆነ ሰው ያውቃሉ? የርሶንም ታሪክ በሚከተለው አድራሻ ያጋሩን፦

ስለ #KEEPITON ቅንጅት

የ #KeepItOn ቅንጅት ከ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥን ወንጀል እየታገሉ ያሉ ከ 300 በላይ ድርጅቶችን በሥሩ ያቀፈ ዓለም አቀፍ አውታረ መረብ ነው። የቅንጅቱ አባልነት በሰብአዊ መብቶች ችግሮች ላይ በዓለም ዙሪያ ለሚሠሩ ለሁሉም የሲቪል ማኅበረሰቦችና ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆኑ ድርጅቶች ክፍት ነው። ከኛ ጋር አብሮ ለመሥራት እንደሚችሉ እዚህ ላይ የበለጠ ይረዱ